Wednesday, 11 December 2013

ኢትዮቴሌኮም የሞባይል ቀፎ ምዝገባ ሊያካሄድ ነው።

ዘገባ በሰንደቅ ጋዜጣ 

ኢትዮቴሌኮም አሁን ባለው የቴሌኮም ማጭበርበር (Telecom fraud) ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ላለው ችግር መፍትሄ ለመስጠት በሞባይል ቀፎዎች ላይ ምዝገባ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነው። ምዝገባው የሚካሄደው የስልክ ቀፎዎቹ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት እና ከሥራ ላይ ያሉትም በመመዝገብ ሲሆን እያንዳንዱ የሞባይል ስልክ ሲመረት በራሱ መለያ ቁጥር ያለው በመሆኑ ምዝገባውም የሚከናወነው በዚሁ መሰረት መሆኑ ታውቋል። በዚሁ ዙሪያ ለሰንደቅ ማብራሪያ የሰጡት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የቴክኒክ አማካሪ ዶ/ር መስፍን በላቸው በቀጣይ በሀገሪቱ ኔትወርክ ሲስተም ውስጥ እንዲሰሩ የሚደረጉት በኢትዮቴሌኮም የተመዘገቡ የሞባይል የስልክ ቀፎዎች ብቻ ናቸው። እንደ ዶ/ር መስፍን ገለፃ የሞባይል ቀፎ ምዝገባን ማካሄዱ ያልተፈቀዱ ሞባይል ቀፎዎች በኢትዮጵያ ኔትወርክ ውስጥ እንዳይሰሩ በማድረግ የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከል የሚያስችል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ደንበኛ ስም በኢትዮቴሌኮም የተመዘገበ ሞባይል መጥፋቱ በባለቤቱ ከተረጋገጠና ኩባንያው ቀፎው እንዳይሰራ እንዲያደርግ ጥያቄ ከቀረበለት ቴሌኮም ኩባንያው ስልኩ እንዳይሰራ የሚያደርግ ቴክኖሎጂንም ይጠቀማል ተብሏል።
     የተመዘገቡ ሞባይል ስልኮች ቢጠፉም እንኳን ሌላ ሰው እንዳይጠቀምባቸው ስለሚደረግ ሞባይሎች ካልተፈታቱና ለሌላ አገልግሎት ካልዋሉ በስተቀር አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውን ዶ/ር መስፍን ገልፀዋል። ኢትዮቴሌኮም በተለይ ከሲም ካርድ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ኩባንያው ሲሞቹን ለአከፋፋዮች ካስረከበ በኋላ አከፋፋዮቹ በበኩላቸው ለተለያዩ ቸርቻሪዎች የሚያከፋፍሉ ሲሆን ይሁንና በየሱቁ ሲም ካርዶችን የሚሸጡ ግለሰቦች የሲም ገዢዎችን አድራሻ በትክክል አጣርተው የተዘጋጀውን ፎርም በመሙላት የሲም ሽያጭ የሚያከናውኑ ባለመሆናቸው ክፍተቶችና ፈጥሮ ቆይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ግለሰቦችን በርካታ ሲሞችን በመግዛት ከውጪ በሚደወሉ ስልኮች ላይ በሀገር ውስጥ መነሻ ኮድ (+251) በመጠቀም የቴሌኮም ማጭበርበር ስራን እየሰሩ ሲሆን በቀጣይ ስራ ላይ የሚውለው የሞባይል ቀፎ ምዝገባና የተመዘገበ የሞባይል ቀፎዎች ብቻ በሀገሪቱ ኔትወርክ ውስጥ እንዲሰሩ ማድረጉ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል። የሚካሄደው የሞባይል ቀፎ ምዝገባ በተለያዩ የሀገሪቱ ድንበሮች በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቀፎዎችንም በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሏል።

No comments:

Post a Comment