Monday, 31 March 2014

ኮምፒውተራችንን ከማልዌር (ሰላይ ሶፍትዌር) መከላከያ ቀላል መንገድ




የዲጂታል ዘመን መምጣት ይዟቸው ከመጡ ጠንቆች መካከል የገዛ ሰላይን ይዞ መዞር ነው። የዴስክቶፕ እና የላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ ስልኮች እንዲሁም ታብሌቶች የስለላ መሣሪያ በመሆን በተለያዩ መንገዶች መረጃዎቻችንን አሳልፈው የሚሰጡባቸው መንገዶች አሏቸው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማልዌር በመባል የሚታወቁ በኮምፒዩተሮቻችን ላይ ተጭነው የሚሰልሉንን የሶፍትዌር ዓይነቶች እንዴት ኮምፒዩተሮቻችን ላይ ከመጫናቸው በፊት በቀላሉ መከላከል እንደምንችል ነው።

ማልዌር ምንድን ነው?

ባለፈው ሰሞን ሲቲዝን ላብ ካወጣቸው መረጃዎች መካከል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞችን በማልዌር ለመሰለል የተደረገው ሙከራ ይገኝበታል። ሙከራው የተደረገው በፒዲኤፍ ፎርማት የተዘጋጁ የሚመስሉ ዶክመንቶችን መረጃ ብለው በመላክ ነገር ግን ማልዌር ሶፍትዌሩ ጋዜጠኞቹ ኮምፒዩተር ላይ ለመጫንና ለመሰለል ነው፡፡ ሙከራው ቢሳካ ኖሮ ጋዜጠኞቹ በቀላሉ የኢሜይል እና የሶሻል ሚዲያ አካውንቶቻቸውን የይለፍ ቃሎች ይሰረቁና የነበራቸው መረጃ ከመበርበሩም በተጨማሪ በነርሱ ስም ሌሎች ሰዎች ጋር በመገናኘት ሰላዮቻቸው ተጨማሪ መረጃ ሊቆፍሩ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ አደጋው ለነርሱም፣ ከነርሱ ጋር የኢሜይል ግንኙነት ላላቸውም ሰዎች ጭምር ነው ማለት ነው፡፡

ይህ በማንኛውም ጋዜጠኛ፣ አራማጅ ወይም ተቃዋሚ ዜጋ ላይ ሊደርስ የሚችል በአምባገነኖች የሚሰነዘር አደጋ የተለመደ አደጋ ነው። ከመንግሥታት በተጨማሪም ግለሰቦች ለተለያዩ ግቦች ማልዌሮችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡