ወደ
ድረ ገጹ ስትገቡ ከፊት ለፊት የምታዩት የሚያስፈራ ሎጎ በሸረሪት ድር፣ በቁልፍና የቁልፍ ጋን ተደጋግፈው የሰሩት የተቋሙ መጠሪያ
ሲታዩ እንደተቋሙ አላማ ደህንነትን ሳይሆን ስጋትን ይፈጥራሉ። (INSA) የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ። “Secured
Cyber for Peace, Development and Democracy” የተቋሙ ሞቶ ነው።
የዚህ
ተቋም ስልጣን አገሪቷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ ብለው የጠረጠሯቸው አካላት ላይ
ካለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ድንገተኛ ምርመራና ብርበራ ያካሂዳል። ይህ ተቋም አደጋ ያመጣሉ ብሎ ያሰበውን ማንኛውም እንደ ኢንተርኔት
ግንኙነት፣ ኮምፒውተሮች፣ የተለያዩ ኔትውርኮች፣ የሬድዮና የተሌቪዝን ስርጭቶች እና ማህበራዊ ድረገጾች ፌስቡክን ጨምሮ አስፈላጊውን
ክትትልና ምርመራ እንዲያደርግባቸው ከተቃዋሚ ፓርቲ አንድ ተወካይ ብቻ ያለው የኢትዮጵያ ፓርላማ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶታል።
የስለላ
መሳሪያዎችን በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች እየገዛ የሚያስገባው የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የኢንተርኔት ግንኙነት መሰለል ብቻ ሳይሆን
በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች እየተገዙ በሚመጡ መሳሪያዎች የአጭር ሞገድ ሬዲዮ ጣብያዎችንና የሳተላይት ቴሌቭዝኖችን በማገድ ዜጎቻቸውን
በስለላ ፋታ ከነሱት ኢራንና ቻይና ተርታ ተመድቧል።
“Secured Cyber for Peace, Development
and Democracy”
ጋዜጠኖች፣
ተቃዋሚዎች እንዲሁም መንግስት ላይ ከፍተኛ ትችት የሚሰነዝሩ ግለሰቦች ያለጥርጥር በዚህ መስሪያ ቤት እይታ ውስጥ ናቸው። የተለያዩ
ጥናቶችና ሪፖርቶች የሚያመለክቱትም የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪዎችን
ሳይሆን ጋዜጠኞችን በመሰለል ስራ ላይ ተጠምዷል። ደህንነቱ
የተጠበቀ የመረጃ መረብ ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ አመጣለሁ የሚለው የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የቅርብ ጊዜ ታሪኩ አሜሪካ
እና አውሮፓ የሚገኙ የኢሳት ጋዜጠኞችን ለመሰለል በመሞከር ድንበር ተሻጋሪነቱን እያሳየ ነው።
ከኢትዮጵያ
መንግስት ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያላት ቻይና ለስለላ የሚረዱ መሳሪያዎችን
ለኢትዮጵያ መንግስት እንደምታቀርብና የኢንተርኔትና የሥልክ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ እንዲሁም ለማፈን የሚጠቅሙ መሳሪያዎችን
በመስራት እስከ አጠቃቀም ድረስ እርዳታ እንደምታደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“እንኳን ዘንቦብሽ......”
ከአፍሪካ
በህዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ እንደ ህዝብ ብዛቷ በቴሌኮም አገልግሎት አቅርቦቷ እያደገች አይደለም። ለዘመናት
ያለተቀናቃኝ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ብቸኛው ኢትዮ ቴሌኮም አገሪቷን ማካለል አቅቶት በዳዴ እየሄደ ይገኛል።
በኢንተርኔትና
በተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ከአፍሪካ ከመጨረሻዎቹ ተርታ የምትሰለፈው ኢትዮጵያ የስለላ ቴክኖሎጂዋ ከአቅሟ በላይ እየሰፋ ይገኛል።
ላለፉት አመታት ሊጠቀስ የሚችል የሽብር ጥቃት አገሪቷ ላይ ባይከሰትም ገዢው ፓርቲ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና የመንግስት ተቺ
ሆነው የቀረቡ ጋዜጠኞችን “ከአሸበሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል” ወይም “መንግስትን በሃይል ለመናድ አሲረዋል” በሚል ሰበብ
ወደ እስር ቤት ወርውሯል።
እነዚህ
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ጋዜጠኞች መንግስት ሲከስ በማስረጃነት ከተጠቀማባቸው ውስጥ የኢሜል እና የስልክ መልዕክት ልውውጦች ናቸው።
የአውራምባ
ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው “ሕገ መንግስትን በሃይል ለመናድ አሲረሀል” ተብሎ የአስራ አራት አመት የእስር ጊዜውን በዝዋይ
ማረሚያ ቤት እያሳለፈ የሚገኘው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ አቃቢ ህግ በማስረጃነት ካቀረበበት መካከል የተቀዳ የስልክ ልውውጥ ይገኝበታል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በስልክ ልውውጥ ውስጥ ሱፍ ልብስ ለመግዛት ሲማከር “ቤዥ ከለር” የሚል ቃል የተጠቀመ ሲሆን “ቤዥ” የምትለዋ
ቃል እንደመገናኛ ኮድ ተቆጥሮ ለእስር ዳርጎታል። ከዚህም የተለየ ብዙ አስቂኝ ማስረጃዎች የሚቀርቡ ሲሆን መንግስት እንዳለው የስለላ
መሳሪያ ብዛት የደህንነት ሀይሎች ብቃትና ንቃት አነስተኛነት ገዢውንም ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ከተለያዩ
አገራትና አለምአቀፍ ተቋማት በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ወቀሳ እየቀረበባት የምትገኘው ኢትዮጵያ መሰረታዊ የዜጎችን ነፃነት በመንፈግም
ተወዳዳሪ እንደሌላት ዳግም እያስመሰከረች ትገኛለች።
መንግስት በመረጃ መረብ ደህንነት ላይ ያለው ሚና:-
የመረጃ
መረብ ደህንነት ጥቅሙ ዜጎችን፣ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶችን ከመረጃ መረብ ዘራፊዎች (በተለምዶ ሃከሮች) እንዲሁም የመረጃ መረብን
በመጠቀም የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ማለትም የመረጃ መረብ ሽብርን ከሚፈፅሙ አካላት የመጠበቅና የመከላከል
ነው።
ጥብቅ
የሆነ የኢንተርኔት ደህንነት ከሚያስፈልጓቸው ተቋማት መካከል ባንክ አንደኛውና ዋነኛው ነው። አለም ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየች
ብትመጣም ኢትዮጰያ በኢንተርኔት የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ተጠቃሚ ባለመሆኗ በገንዘብ ዝውውር ወቅት በሀከሮች የሚደረግ ዝርፊያ
አያሳስባትም።
ከላይ
የተጠቀሱት ችግሮች እንዳሉ ሆነው አንገብጋቢው ጥያቄ ግን መሆን ያለበት “መንግስት ዜጎችን ከሀከሮች፣ ከመረጃ መረብ ሽብርተኞች
ለመከላከል ምን ያህል ርቀት መጓዝ አለበት?” የሚል ነው። ይህ የደህንነት
ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ በአንባገነናዊ ስርአት ውስጥ ለሚዋትቱ አገሮች የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመጣስና የስልጣን ወንበርን ያለተቀናቃኝ
ለማመቻመች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
“የአገርን
ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል” እና “በሽብር ተግባር በመሳተፍ” የሚሉ ውንጀለዎች አንባገነኖች ተቀናቃኛቸውን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብአዊ
መብት አራማጆችን እስርቤት የማጎሪያ መሳሪያ እየሆነ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥም የመረጃ ደህንነት ኤጀንሲ ከተሰጠው ሚና ውስጥ ያለፍርድ
ቤት ትእዛዝ ማንኛውንም ኮምፒተርና ሌሎች ተያያዥ መሳሪያዎች መመርመር የሚያስችል ስልጣን ነው። ይህ መስሪያ ቤት መሰረተ ልማቶችን፣
ተቋማትንና የዜጎችን ደህንነት እየጠበቀ ሳይሆን ለዜጎች የደህንነት ስጋት እየሆነ ይገኛል።
የመረጃ
መረብ ነፃነት በኢትዮጵያ ውስጥ አለመኖሩ እንደአመላካች ሊወሰድ የሚገባው የአንድ ልእዋለዊ አገር ተቋም እንደ ተራ የመረጃ መረብ
ዘራፊ አህጉር ተሻግሮ የግለሰቦችን ዳታ ለመዝረፍ መሞከሩ ነው። አነሰም በዛም የመንግስት ተቺ ሆነው የቀረቡ ግለሰቦችና ተቋማት
“የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ” የሚል ታርጋ እየተለጠፈባቸው በስለላ ወጥመድ ውስጥ እንደሚገኙ አያጠራጥርም።
የኢትዮጵያ
የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) በእስከአሁን ጉዞው ከመረጃ ጠለፋና ከመረጃ መረብ ሽብር ጋር በተያያዘ አንድም ግለሰብ
ላይ ክስም ማስረጃም አላቀረበም። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓረቲ አመራሮች ተከሰው
ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግን “በተከሰሱበት ወንጀል መሳተፋቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለኝ።” በማለት በስለላ የተገኙ ግለሰቦቹ የተለዋወጧቸው
የኢሜልና የስልክ ግንኙነቶች በማስረጃነት ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል።
No comments:
Post a Comment